አጫጭር መጣጥፎች

በሀገራችንም ሆነ በተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች በማህበረሰቡ ውስጥ ባሉ ወንጀል አድራጊዎች የሚተገበሩ የተለያዩ ወንጀሎች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ የጠለፋ ወንጀል ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ወንጀል በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ በሰው ነፃነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተብለው ከተደነገጉት ውስጥ የሚመደብ የወንጀል ዓይነት ነው፡፡ ጠለፋ በሁለቱም ፆታዎች ላይ ሊፈፀም የሚችል ሲሆን በዋነኛነት በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈጸም ነው፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ ስለ ጠለፋ ምንነት፣ የጠለፋ ድርጊትን ሽፋን የሰጡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን፣ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት እና በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ ክልከላ የተደረገባቸውና የወንጀል ቅጣትን የሚያስከትሉ ድርጊቶችን እንመለከታለን፡፡

የጠለፋ ወንጀል ምንነት እና ጉዳቱ
ጠለፋ ማለት ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ እና ከሌሎች የሀገራችን ሕጎች አንፃር ሲታይ በግዳጅ ጋብቻ ለማስፈጸም ከሚደረግ ድርጊት በተጨማሪ ለጉልበት ብዝበዛ፤ ለወሲብ፤ ለሽብር ዓላማ እና ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት የሚደረግ ድርጊት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ እንደሌሎች ጥቃቶች ሁሉ ድርጊቱ በሀገራችን በተለይም በገጠር አካባቢ ተስፋፍቶ የሚታይ ነው፡፡ ተጠላፊዎቹ በተለይም የምትጠለፈው ሴት ድብደባ እና እንግልት ስለሚደርስባት (ቸው) ለአካል ጉዳት ወይም ሞት፣ ደስተኛ ልሆነና ያልተረጋጋ ሕይወት (ጋብቻ) መኖር፣ ጭንቀት፣ ትምህርት (ሥራ ማቋረጥ) ወዘተ… የመሳሰሉትን ጉዳቶች ያስከትላል፡፡ የጠለፋ ወንጀል በዋናነት ሰውን መጥለፍ እና ሴትን መጥለፍ በሚል በኢ.ፌዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 586 እና 587 የተደነገገ ሲሆን የማክበጃ ምክንያቶቹ በዚሁ ሕግ አንቀጽ 590 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡
የጠለፋ ወንጀል በዓለም አቀፍ ስምምነቶች
ለሰው ልጆች ሁሉ ሰብዓዊ መብት ዕውቅና የሰጠው ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መገለጫ አንቀጽ 3 "እያንዳንዱ ሰው የሕይወት፣ የነፃነትና የደህንነት መብት አለው፡፡ ″ ያለ ሲሆን በአንቀጽ 2 ላይ ደግሞ "ማንኛውም ሰው በዘር፣ ቀለም፣ ጾታ፣ እና ሌሎች ምክንያቶች ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግበት በመግለጫው ውስጥ የተቀመጡትን መብቶችና ነፃነቶች የማግኘት መብት አለው" በማለት ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ሴቶች እና ህፃናት በስምምነቱ የተካተቱ መብቶች ተጠቃሚ ለመሆን በፆታና በእድሜያቸው ምክንያት ከሚደርሱባቸው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ መብት እንዳላቸው መረዳት ይቻላል፡፡
የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተርም በአንቀጽ 6 ላይ ″ማንኛውም ሰው ነፃነቱና አካላዊ ደህንነቱ ተጠብቆለት የመኖር መብት አለው፡፡ ቀድሞ በሕግ በተደነገጉት ሁኔታዎችና ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ነፃነቱን እንዲያጣ ሊደረግ አይችልም" በማለት ደንግጓል፡፡
በሴቶች ላይ የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ልዩነት ወይም አድሎ ለማስወገድ የወጣ ስምምነት (The Convention on the Elimination of All Forms of Discrimination against Women (CEDAW), 1979) አንቀፅ 2 (ረ) እንደሚደነግገው በሴቶች ላይ አድልዎ የሚፈጥሩ ልማዶች ለማስወገድ ነባር ሕጎችን፣ ደንቦችን ለማሻሻል ወይም ለመሻር ጨምሮ ሁሉንም ተገቢ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስወገድ የተሰጠ መግለጫ (Declaration on the Elimination of Violence Against Women (DEVAW),1993) በአንቀፅ 4 ስር እንደሚያስቀምጠው የስምምነቱ አባል መንግስታት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ማውገዝ እንዳለባቸው ግዴታ የሚጥል ሲሆን በተጨማሪም ይህን ግዴታቸውን ላለመወጣትና ጥቃቶቹን ላለማስወገድ ማንኛውንም ባህል፣ ወግ ወይም ሃይማኖት እንደ ምክንያት ማንሳት አይችሉም፡፡ ለህፃናት መብት ጥበቃ በሚያደርገው በተባበሩት መንግስታት ደርጅት የህፃናት መብቶች ስምም (Convention on the Rights of the Child,CRC ) የቻርተሩ ተዋዋይ አገራት የሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራት በቻርተሩ ለተደነገጉ መብቶች፣ ነጻነቶችና ግዴታዎች ዕውቅና የመስጠት፤ የቻርተሩ ድንጋጌዎችን ተፈጻሚ ለማድረግ በቻርተሩና በየሕገ-መንግሥቶቻቸው በተመለከቱ ድንጋጌዎች መሠረት እንደ አስፈላጊነቱ የሕግ ማውጣትን እና ሌሎች እርምጃዎች የመውሰድ ግዴታ አለባቸው፡፡ በየአፍሪካ ሕፃናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር አንቀጽ 29 መሠረት አባል ሀገራት “የሕፃናቱን ቤተሰብ ወይም ሕጋዊ አሳዳሪ ጨምሮ በማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ ወይም በማንኛውም መንገድ ሕፃናትን በኃይል አስገድዶ መውሰድን፣ መሸጥን ወይም በሕፃናት መነገድን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለባቸው″ በማለት ደንግጎ ይገኛል፡፡
ጠለፋ በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 35 (4) ሴቶችን የሚጨቁኑ ወይም በአካላቸው ወይም በአዕምሮአቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጎች፣ ወጎችና ልማዶች የተከለከሉ መሆናቸውን እና ሴቶች ከጎጂ ባህል ተፅዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን መንግስት ማክበር እና ማስከበር እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በሌላ በኩል የህፃናትን መብት በሚደነግገው የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 36 መሰረት ህፃን በህይወት የመኖርን መብት ጨምሮ ጉልበትን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣ በትምህርቱ፣ በጤናውና በደህንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሥራዎች እንዲሰራ ያለመገደድ ወይም ከመስራት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ ሕገ- መንግስት ዝርዝር ጉዳዮችን የማያካትት ሕግ በመሆኑ በሰው ነፃነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዝርዝር ሁኔታዎች በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ ተካተው ይገኛሉ፡፡ በዚሁ መሰረት የወንጀል ሕጉ የተከለከሉ ድርጊቶችን በመዘርዘር የሚያስከትሉትንም ቅጣት ያስቀምጣል፡፡ በወንጀል ሕጉ ከተቀመጡት ክልከላዎች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ሰውን መጥለፍ (አንቀጽ 586) ፡- ማንም ሰው በኃይል ሌላውን ሰው አፍኖ የወሰደ እንደሆነ፣ ወይም ይህንኑ ድርጊት የፈፀመው በዛቻ፣ በማስገደድ፣ በተንኮል፣ በማታለል ወይም በማናቸውም ሌላ አኳኋን የሌላውን ሰው ፈቃድ ካገኘ በኋላ እንደሆነ ከ7 (ሰባት) ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ሴትን መጥለፍ (አንቀጽ 587) ፡- ማንም ሰው አንዲት ሴትን አገባታለሁ በሚል አሳብ በኃይል የጠለፈ እንደሆነ፣ ወይም ይህንኑ ድርጊት የፈፀመው በማስፈራራት፣ በዛቻ፣ በተንኮል ወይም በማታለል ፈቃደኛ እንደትሆን ካደረገ በኋላ እንደሆነ ከ3 እስከ 10 ዓመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ በተለይም የጠለፋ ድርጊቱን ተከትሎ አድራጊው ሴትዮዋን አስገድዶ የደፈረ እንደሆነ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ስለ አስገድዶ መድፈር በተመለከተው ድንጋጌ ( አንቀጽ 620) መሠረት በተጨማሪ ይቀጣል፡፡ የጠለፋ ድርጊት ተከትሎ በጠላፊውና በተጠላፊዋ መሀከል ጋብቻ መፈፀሙ የወንጀል ተጠያቂነትን አያስቀርም፡፡ ጠላፊውን ከወንጀል ተጠያቂነቱ ሌላ ተጠላፊዋ (ተበዳይዋ) በጠለፋው ድርጊት ለደረሰባት የኅሊና እና ቁሳዊ ጉዳት አግባብ ባላቸው የፍትሐብሔር ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ካሣ የመጠየቅ መብት አላት፡፡ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን መጥለፍ (አንቀጽ 589)፡- ማንም ሰው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን በኃይል አፍኖ የወሰደ አንደሆነ፣ ወይም ይህንኑ ድርጊት የፈፀመው በዛቻ፣ በማስገደድ፣ በተንኮል፣ በማታለል ወይም በማናቸውም ሌላ አኳኋን የልጁን ፈቃድ ካገኘ በኋላ እንደሆነ ከ5 ዓመት እስከ 15 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ እንዲሁም ማንም ሰው ወላጅን ወይም የአሳዳሪውን የማሳደግ ወይም የመጠበቅ ሕጋዊ መብት ለማሳጣት በማቀድ ለአካለመጠን ያልደረሰ ልጅ የወሰደ፣ የጠለፈ ወይም ያለአግባብ ይዞ ያስቀመጠ እንደሆነ ከ5 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ የአዕምሮ ሕመምተኛ የሆነችን ወይም የመከላከል አቅም የሌላትን ሴት መጥለፍ (አንቀጽ 588) አንደሚያስቀጣ ተደንግጓል፡፡ ማንም ሰው ያበደችን፣ የአዕምሮ ጉድለት ወይም ዝግመት ያለባትን፣ ሕሊናዋ የሳተችውን ወይም ራሷን ለመከላከል ወይም ጥቃትን ለመመለስ የማትችለውን ወይም ራሷን ለመከላከል እንዳትችል የተደረገችውን ሴት ሁኔታ እያወቀ አስቦ የጠለፈ እንደሆነ ከ5 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ወንጀሉን የሚያከብዱ ሁኔታዎች (አንቀጽ 590) ፡- የጠለፋው ድርጊት በተፈፀመበት ጊዜ ዛቻው፣ ማስገደዱ፣ የመወሰን ችሎታን ማሳጣቱ፣ ከሕግ ውጭ ይዞ ማስቀመጡ ወይም መጥለፉ የተፈፀመው ፡- ሀ. የማይገባ ጥቅም ከተጎጀው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም ለግልሙትና ወይም ለአመንዝራነት ተግባር ወይም ለንጽህና ክብር ተቃራኒ ለሆነ ተግባር ለመጠቀም ወይም ለዚሁ ተግባር
አሳልፎ ለመስጠት በማሰብ፣ ወይም
ለ. ተጎጅውን ለመበዝበዝ ወይም ወጆ ለመቀበል፣ ወይም ሐ. የተለየ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እንደሆነ፣ ወንጀሉ የከበደ ሆኖ በሚከተሉት ድንጋጌዎች እንደሚከተለው ይሆናል፡-
2. ወንጀሉ፡-
ሀ. ዛቻ ወይም ማስገደድ (አንቀጽ 580- 582) ሲሆን ከ 3 ወር እስከ 5 ዓመት መድረስ የሚችል ቀላል እስራት፣
ለ. የመወሰን ችሎታን ማሳጣት ወይም ከሕግ ውጭ ይዞ ማስቀመጥ ( አንቀጽ 583 እና 585) ሲሆን ከ7 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት፣
ሐ. መጥለፍ ( አንቀጽ 586 እና 587) ሺኆን ከ 5 ዓመት እስከ 15 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት፣
መ. የአዕምሮ ሕመምተኛ የሆነችን ወይም ለመከላከል አቅም የሌላትን ሴት መጥለፍ (አንቀጽ 588) ሲሆን ከ7 ዓመት እስከ 20 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት ወይም
ሠ. ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን መጥለፍ (መስረቅ) አንቀጽ 589 ሲሆን ከ10 ዓመት እስከ 25 ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ አስራት ያስቀጣል፡፡
በአጠቃላይ ጠለፋ በአብዛኛው በገጠር አልፎ አልፎ በከተማ አካባቢ ሊፈፀም የሚችል የወንጀል ኃላፊነትን የሚያስከትል ድርጊት በመሆኑ መንግስት ከሚያደርገው የሕግ ጥበቃ ጎን ለጎን ዜጎች ድርጊቱ በሰው ነፃነት አለፍ ሲልም ህይወት እና አካል ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት በመገንዘብ ድርጊቱ እንዳይፈጸም የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ! https://t.me/jlrtinet
ሙሉ መረጃ ለማዉረድ ከህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ነው!

በሥራ ቦታዎች ፆታዊ ትንኮሳዎች በአብዛኛው በሴቶች ላይ እንደሚፈፀሙ መስማት አዲስ አይደለም፡፡ ሆኖም በፈፃሚዎች በኩል ድርጊቱ በተለምዶአዊ ሁኔታ ትክክል እንደሆነ አድረጎ የመውሰድና በተጎጂዎችም በኩል ድርጊቶቹ ፆታዊ ትንኮሳ መሆናቸውን ተረድቶ መፍትሄ የመፈለግ ውስንነቶች ይስተዋላሉ፡፡ በዚህ አጭር ፅሁፍ በፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1164/2010 እና በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ለፆታዊ ትንኮሳ የተሰጠውን ትርጓሜ እና የሚስከትለውን ተጠያቂነት በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡

የፆታዊ ጥቃት ምንነት
በሀገራችን ሰራተኞች አስመልክቶ በፌደራል ደረጃ የወጡ ሁለት አዋጆች ያሉ ሲሆን እነዚህም የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1164/2010 እና የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ናቸው፡፡ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ እራሱን ችሎ በአዋጅ ወይም በደንብ በተቋቋመና ከመንግስት በሚመደብለት በጀት በሚተዳደር የፌደራል መንግስት መሥሪያ ቤት በቋሚነት በሚሰሩ ሰራተኞች (በልዩ ሁኔታ እንደማይፈፀምባቸው ከተገለፁት ውጪ) ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ሲሆን የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ የግሉን ዘርፍ ጨምሮ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል በሚደረግ በቅጥር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ነው፡፡ በሥራ ቦታ ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ትንኮሳ በተመለከተ በሁለቱም አዋጆች በዝርዝር ተካቶ ይገኛል፡፡
በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/11 በአንቀፅ 2/11 እና 12 መሰረት “ወሲባዊ ትንኮሳ” ማለት በንግግር፣ በምልክት ወይም በሌላ ማናቸውም አድራጎት አንዱ ሌላውን ከፈቃዱ ውጭ ለወሲባዊ ተግባር ፈቃደኛ እንዲሆን ማባበል፣ መገፋፋት፣ ተፅዕኖ ማሳደር ነው፡፡ እንዲሁም “ወሲባዊ ጥቃት” ማለት ኃይል የተቀላቀለበት ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም የዚሁ ድርጊት ሙከራ ነው በማለት ትርጉም ሰጥቶት ይገኛል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 ለፆታዊ ትንኩሳ ትርጉም ከመስጠት ባሻገር ዝርዝር ተግባራትን እና ድርጊቶቹን ለማስፈፀም እንደቅድመ ሁኔታ ሊገለፁ የሚችሉ ጉዳዮችን አስቀምጧል፡፡ ይኸውን በአዋጁ አንቀፅ 2/13 ሥር እንደተደነገገው “ፆታዊ ትንኮሳ” ማለት በሥራ ቦታ የሚፈፀም ሆኖ ከሌላው ወገን ፈቃድ ውጪ የሚቀርብ የወሲብ ሀሳብ ወይም ጥያቄ ወይም ሌላ ወሲባዊ ተፈጥሮ ያለው የቃል ወይም የአካል ንኪኪ ተግባር ሲሆን ይህም
  1. ከሌላው ወገን ፈቃድ ውጪ የመሳም፣ የሰውነት አካልን የመዳሰስ፣ የመጎንተል ወይም የመሳሰለውን የሰውነት ንክኪ የመፈፀም ድርጊት
  2. ወሲብ አዘል በሆነ ሁኔታ ተጠቂውን መከታተል ወይም እንቅስቃሴውን መገደብ
  3. ለቅጥር፣ ለደረጃ እድገት፣ ለዝውውር፣ ለድልድል፣ ለሥልጠና፣ ለትምህርት፣ ለጥቅማ ጥቅሞች ወይም ማንኛውንም የሰው ሀብት ሥራ አመራር ተግባር ለመፈፀም ወይም ለመፍቀድ ወሲብን እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥን ያካትታል፡፡
ፆታዊ ትንኮሳ የሚያስከትለው ተጠያቂነት
በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር በአዋጁ አንቀፅ 14 ሥር እንደተደነገገው በሥራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት መፈፀም ከተከለከሉ ተግባራት አንዱ ሲሆን ሠራተኛው (ወንድም ሆነ ሴት) በአሠሪው ወይም በሥራ መሪው ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት የተፈፀመበት እንደሆነ ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውልን ለማቋረጥ የሚያስችል አንዱ ምክንያት ነው (የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/11 አንቀፅ 32/1/ለ)፡፡ ይኸውም ሰራተኛው ለተፈፀመበት ጥቃት እንደ ጥቃቱ አይነት አግባብ ባለው የወንጀል ህግ መብቱን ማስከበር የሚችል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሰራተኛው የሥራ ውሉን በሚያቋርጥበት ወቅት ተገቢውን ካሳ ማግኘት ያስችለዋል፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 41/2 ሥር እንደተገለፀው ሰራተኛው ሥራውን ለማቋረጥ የተገደደው በተፈፀመበት ፆታዊ ትንኮሳ ሳቢያ ከሆነ ከሥራ ስንብት ክፍያው በተጨማሪ የቀን ደመወዙ በ90 ተባዝቶ ይከፈለዋል፡፡
በተያያዘ በፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 70/13 እና 69 ሥር እንደተደነገገው በሥራ ቦታ ላይ ፆታዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት መፈፀም ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት ከሚያስከትሉ ጥፋቶች አንዱ ሲሆን እስከ 3 ወር ደሞዝ የሚደርስ መቀጮ፣ እስከ 2 ዓመት ለሚደርስ ጊዜ በሥራ ደረጃ እና ደሞዝ ዝቅ ማድረግ ወይም ከሥራ እስከመሰናበት የሚደርስ ቅጣትን ሊያስከትል ይችላል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1164/2010 እና የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 የፆታዊ ትንኮሳን ትርጓሜ በመደንገግ የሚያስከትለውን ተጠያቂነት በግልፅ ያስቀመጡ በመሆኑ ፈፃሚዎች በአዋጆቹ የተመለከቱ እርምጃዎች የሚወሰዱባቸው ከመሆኑም በተጨማሪ አግባብ ባለው የወንጀል ህግ የሚያስጠይቁ ተግባራት በወንጀል ጭምር የሚያስጠይቁ ናቸው፡፡ ስለሆነም ህብረተሰቡ ከመሰል ድርጊቶች መታቀብ እና ድርጊቶቹ ተፈፅመው ሲገኙም ፈፃሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡
መረጃውን ከፍትሕ ሚኒስቴር አገኘነው፡፡ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ! https://t.me/jlrtinet
ሙሉ መረጃ ለማዉረድ

መረጃው፡- የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ነው!

ፆታዊ ትንኮሳ የሚያስከትለው ተጠያቂነት
ህግ የሚለው ቃል በማህበረሰቡ ዘንድ በስፋት የሚታወቅ ቃል ነው፡፡ በተለይ ህግ አስገዳጅ መሆኑን የሚረዳው ለመሆኑ ቀደም ባለው ጊዜ በየዕለት ኑሮ ፀብ ሲገጥመው እንኳን “በህግ አምላክ” ብሎ ፀብ የማብረድ ልምድ የነበረው መሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ሆኖም ማህበረሰቡ ህግን የሚረዳው በተለምዶአዊው አረዳድ እንጂ የዘርፉ ባለሞያዎች በሚረዱበት መልኩ አይደለም፡፡
በመሰረቱ ህግ ለሚለው ቃል ትርጓሜ መስጠት ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ ምሁራን ቃሉን በተለያየ መንገድ የሚገልፁት በመሆኑ ነው፡፡ እንዲሁም የቃሉ ፍቺ ሊደረስባቸው በሚፈለጉት የተለያዩ ዓላማዎች ምክንያት ሊለያይ ይችላል።
ለህግ ቃላት ትርጉም በመስጠት የሚታወቀው ብላክስ ሎው የህግ መዝገበ ቃላት በተሻሻለው ስድስተኛ እትሙ (Black’s Law Dictionary, 6th ed.,) ለህግ ትርጉም ሲሰጥ law is “a body of rules of action or conduct prescribed by controlling authority, and having binding legal force, which must be obeyed and followed by citizens subject to sanctions or legal consequence is a law.” ወደ አማርኛ በግርድፉ ሲመለስ ስልጣን ባለው አካል የተደነገገ የተግባር ወይም የምግባር ደንብ እና አስገዳጅ የህግ ኃይል ያለው አካል ነው። ይህንንም ዜጎች ሊታዘዙት እና ሊከተሉት የሚገባ ሆኖ ማዕቀብ ወይም ህጋዊ ውጤት የሚጥል ህግ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
በመሆኑም የአንድ ሀገር ሕግ፡- ሰላምን ለማስጠበቅ፣ ነባራዊ ሁኔታውን ለማስጠበቅ (maintain the status quo)፣ የግለሰብ መብቶችን ለማስጠበቅ፣ አናሳዎችን ከብዙኃን ለመከላከል ( protect minorities against majorities)፣ ማኅበራዊ ፍትህን ለማስፈን( promote social justice) እና ሥርዓት ያለው ማህበራዊ ለውጥ እንዲኖር ለማድረግ ( provide for orderly social change) ያገለግላል።
የህግ መሰረታዊ ባህሪያት
የህጎችን የተለመዱ ባህሪያት እና ተፈጥሮ መፈተሽ የህግ ጽንሰ-ሀሳብን ለመገንዘብ የሚረዳ ሲሆን ከእነዚህ ባህሪያት እና ተፈጥሮዎች መካከል እንደ ወሰኝ ወይም አስፈላጊ የሚታሰቡት አጠቃላይነት(ህግ በሁሉም ሰው ላይ በተመሳሳይነት (uniformity) እና እኩልነትን (Equality) የሚፈፀም መሆኑ)፣ መደበኛነት (ህግ ማህበራዊ ባህሪን በመፍቀድ፣ በማዘዝ ወይም በመከልከል ልማዶችን የሚፈጥር መሆኑ) እና ማዕቀብ ወይም ቅጣትን (ህግን ያላከበረ ቅጣት የሚጠብቀው መሆኑን) ያካትታሉ፡፡
ህግን አለማወቅ እና የህግ ስህተት ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑ
በወንጀልም ሆነ በፍትሐ ብሄር ጉዳይ ህጎቹ ስልጣን ባለው የህግ አውጪ አካል ወጥተው ከፀደቁበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንደሚውሉ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ዜጎች የህጎቹን መኖር ወይም መውጣት የማወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ይኸውም ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም የሚለው የህግ መርህ በላቲን Ignorantia juris non excusat ወይም በእንግሊዘኛ "ignorance of the law excuses not" ከሮማውያን ህግ የተወሰደ ሲሆን ህግን የማያውቅ ሰው ይዘቱን ባለማወቅ ብቻ ህጉን በመተላለፍ ከተጠያቂነት ሊያመልጥ እንደማይችል የሚገልጽ የህግ መርህ ነው። እንዲሁም የህግ ስህተት (mistake of law) ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ተፈጻሚነት ያለው ሕግ እንዴት እንደሚተገበር የሚይዙትን የአረዳድ ስህተቶችን የሚያመለክት የሕግ መርህ ነው። ‘ህግን አለማወቅ’ እና ‘የህግ ስህተት’ የሚሉት ቃላቶች በህጋዊ እይታ ውስጥ ተመሳሳይ ትርጉም የማይሰጡ ሲሆን አለማወቅ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ አጠቃላይ የእውቀት ያለመኖርን ያመለክታል። ማሳሳት ግን እውቀትን ተቀብሎ ወይም እውቀት እንዳለ አምኖ ነገር ግን የተሳሳተ መደምደሚያን ላይ መድረስን ያሳያል። ይሁንና ህግን አለማወቅም ሆነ የህግ ስህተት ከተጠያቂነት እንደማያድን እንደ አንድ የህግ መርህ ይወሰዳል፡፡
ህግን አለማወቅ እና የህግ ስህተት ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑ መርህ ምክንያት (rationale for "ignorance of the law excuses not" principle)
በመሠረቱ አንድ ሰው ህግን ከጣሰ ህጉን ስለመጣሱ ምንም እውቀት ባይኖረውም ተጠያቂ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ሰዎች ህጉን አላውቀውም በማለት ድርጊታቸውን ሊከላከሉ እንደማይችሉ ያመለክታል፡፡ የዚህ ህግ መርህ ምክንያት( rationale) አለማወቅ ሰበብ ቢሆን ኖሮ ምንም እንኳን ያ ሰው ህጉ መኖሩን ቢያውቅም በወንጀል ህግ ወይም በፍትሐ ብሄር ጉዳይ ቢከሰስ ህጉን አላወኩም በማለት ከተጠያቂነት ማምለጫ እንዳይሆን በሚል ነው፡፡ በመሆኑም ከመርህ በስተጀርባ ያለው ምክንያት አለማወቅ ሰበብ ከሆነ ማንኛውም በወንጀል ወይም በፍትሐ ብሄር የተከሰሰ ሰው ተጠያቂነትን ለማስወገድ አላዋቂ ነኝ ሊል ይችላል የሚል ነው። ስለዚህ ህጉ የቱንም ያህል አጭር ጊዜ ቢቆይ ሁሉም ህጎች በስልጣኑ ውስጥ ላለ ለእያንዳንዱ ሰው ተፈፃሚ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
በኢትዮጵያም ህግን አለማወቅ ወይም የህግ ስህተት ከተጠያቂነት እንደማያድን በወንጀል ህጉ አንቀፅ 81 ስር ተደንግጓል፡፡ በዚሁ መሰረት ሕግን አለማወቅ ወይም በህግ ላይ መሳሳት መከላከያ ሊሆን እንደማይችል ያስቀምጣል፡፡ በሌላ በኩል በፍትሐ ብሄር ህግ አንቀፅ 2035/1 እና 2 ስር አንድ ሰው በህግ ላይ በትክክል የተገለፀውን ድንጋጌ፣ ልዩ ደንብና ሥርዓት የጣሰ እንደሆነ ጥፋተኛ እንደሆነ እና ህግን አለማወቅ ይቅርታ ሊያስገኝ የማይችል መሆኑ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
የህግ መኖር ማወቅ የሚቻልበት መንገድ
ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም የሚል የህግ መርህ ተቀባይነት አለው ማለት ሁሉም ሰው ህግ የማወቅ ግዴታ እንዳለበት እና የህግን መኖር ያውቃል የሚል ግምት እንደሚወሰድ ያመለክታል፡፡ ታዲያ ሁሉም ሰው ህግን የተማረ ሊሆን የማይችል በመሆኑ እንዲሁም ህግን ቢማር እንኳ ሁሉን ህግ በተገቢው ሁኔታ ያውቃል ማለት ተጨባጭ (realistic) የማይመስል በመሆኑ የህግን መኖር እንዴት ማወቅ ይቻላል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡
የህግን መኖር በተለያዩ መንገዶች ማወቅ ይቻላል፡፡ ይኸም በዋናነት ህጎች የሚፀኑበትን ጊዜ ከሚገነግጉ ድንጋጌዎች ሲሆን ህግ የሚፀናበት ጊዜ በተለያዩ ህጎች ላይ በተለያየ ሁኔታ ተገልፆ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረት ህጉ ወይም አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከሚወጣበት ቀን ጀምሮ የሚፀና ይሆናል፣ ህጉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ ተፈፃሚ ይሆናል እና የተወሰነ ቀን በማስቀመጥ ከዛ ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን ሊደነገግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግስት በህዳር 29/1987 የፀደቀ ሲሆን ከነሐሴ 15/1987 ጀምሮ በሥራ ላይ እንደሚውል እና የፀና እንደሚሆን በመደንገግ ህጉ የሚፀናበትን ጊዜ በዚህ መልኩ አውጇል ፡፡ በመሆኑም ህጎቹ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታውጀው ከፀደቁበት ቀን ጀምሮ ወይም በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ በህብረተሰቡ ይታወቃሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
ህግን አለማወቅ እና የህግ ስህተት ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑ መርህ የማይፈፀምበት ልዩ ሁኔታ
ህግን አለማወቅ እና የህግ ስህተት ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑ መርህ የማይፈፀምበት ልዩ ሁኔታ የተፈጠረው በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍርድ ቤቶች በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ነው። ፍርድ ቤቶች የህግ አለማወቅ እንደ ሰበብ የተቀበሉት የህግ ጥሰት ሆን ተብሎ ያልተፈፀመ ወይም ያለጥፋት ሲጣስ ሆኖ በዚህ ጊዜ ቅጣት ለመጣል ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ስለሆነም የሕግ ስህተት እንደ መከላከያ የሚሠራው የሕግ ስህተቱ ሐቀኛ ሆኖ በቅን ልቦና ሲሠራ ነው። እንዲሁም የተከሳሽ ህግን አለማወቅና ስህተት ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ አጠቃላይ ህግን አለማወቅ እና የህግ ስህተት ከተጠያቂነት አያድንም የሚለው መርህ ተፈፃሚ አይሆንም ማለት ነው፡፡
በተመሳሳይ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ወንጀል ህግ አንቀፅ 81/2 ስር እንደተደነገገው ድርጊቱን ለመፈፀም መብት ያለው መሆኑን በቅን ልቦና ለማመንና እንደዚህ ባለ የተሳሳተ እምነት ላይ ለመገኘት በቂና እርግጠኛ ምክንያት ያለው ሆኖ ለተገኘ ወንጀለኛ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ሊያቀልለት እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን የሚወስነው ከስህተት የደረሰበትን ምክንያት በተለይም የስህተትና የነገሩን ሁኔታ በመገመት ነው፡፡ በተጨማሪ ምክንያት ሊገኝበት በሚችልና ፍፁም በሆነ አለማወቅና ቅን ልቦና እንዲሁም ወንጀሉን የማድረግ አሳብ መኖሩን በግልፅ በማይታይባቸው የተለዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ከቅጣት ነፃ ለማድረግ እንደሚችል የወንጀል ህጉ ይደነግጋል፡፡
በአጠቃላይ ህግ የሰዎችን የእለት ተዕለት ተግባር በመግዛት ሰላማዊ ኖሮ እንዲኖሩ የሚያስችል አንዱ መሳሪያ በመሆኑ ሰዎች ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት እንደማያድን እና መከላከያ ሊሆን እንደማይችል በማወቅ በተቻለ መጠን ህገ ወጥ ከሆኑ ተግባራት እራሳቸውን ማራቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃዎች የቴሌግራም ቻናላችንን ይወዳጁ! https://t.me/jlrtinet

መረጃው፡- የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ነው!

(በሀገራችን ኢትዮጵያ የተሽከርካሪ አደጋ በእጅጉ እየበዛ እና ከፍተኛ የሆነ ሞት፣ አካል ገዳት እና የንብረት ጉዳት እያስከተለ ይገኛል፡፡ ከአደጋው አስከፊነትና ከሰብአዊነት አንፃር የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ይገባቸዋል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ጉዳት አድራሹ በመሰወሩ ምክንያት ላይታወቅ የሚችልበት እድል ከመኖሩም በላይ ቢታወቅም እንኳን በወቅቱ ወጪውን ለመሸፈን የሚያስችል አቅም የሌለው የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ ይህም ተጎጂዎችን ለተጨማሪ ጉዳትና እንግልት ሊዳርግ ይችላል፡፡
ይህንን ችግር ለማቃለል የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን አስገዳጅ በሆነ መልኩ በሕግ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን አዋጅ ቁጥር 799/2005 በአሁኑ ሰዓት በሥራ ላይ የሚገኝ ሕግ ነው፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ የሕጉን ይዘት እንዳስሳለን፡፡

የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ምንነት
መድን ወይም ኢንሹራንስ ስለሚለው ቃል ከተለያየ አቅጣጫ በማየት ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ፡፡ ከግለሰቦች መነሻ ነጥብ ተነስቶ የሚሰጠው ትርጉም የመጀመሪያው ሲሆን እሱም “አንድ ሰው በንብረቱ፣ በህይወቱ ወይም በአካሉ ላይ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሊያጋጥም በሚችል አደጋ ምክንያት የሚደርስ በገንዘብ የሚለካ ጉዳትን ለኢንሹራንስ ድርጅት ማስተላለፊያ መንገድ ነው፡፡” ሁለተኛው መነሻ ነጥብ ከኢንሹራንስ ሰጪው ድርጅት በመነሳት ሲሆን “ኢንሹራንስ ሰጪው በአደጋ ምክንያት የሚያጋጥምን ኪሳራ ለተመሳሳይ አይነት አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች የሚያከፋፍልበት መንገድ ወይም ዘዴ ነው፡፡”
በሀገራችንም በነባሩ የንግድ ሕግ አንቀጽ 654(1) ላይ “የኢንሹራስ ውል ፖሊሲ ማለት ኢንሹራንስ ሰጪ የሚባለው በአንድ ወይም በብዙ የተመደበውን የኢንሹራንስ መግቢያ ዋጋ (ፕርምየም) ተቀብሎ በውሉ የተመለከተው አደጋ በደረሰ ጊዜ ኢንሹራንስ ለገባው ሰው የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል ግዴታ የሚገባበት ነው፡፡” በማለት ትርጉሙን አስቀምጧል፡፡ ይህ የጠቅላላው የመድን ውል ትርጓሜ ሲሆን የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድንን በተመለከተ ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 799/2005 አንቀፅ 2( እና (10) ስር ከተሰጡት ትርጉሞች ተነስተን መረዳት እንችላለን፡፡ በዚህም መሰረት “የመድን [ውል] ማለት የመድን ገቢው ተሸከርካሪ በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው የሞት አደጋ፣ የአካል ጉዳት ወይም የንብረት ኪሳራ ካሳ ለመክፈል እና የአስቸኳይ የሕክምና አገልግሎት ክፍያን ለመፈፀም መድን ሰጪው ውለታ የሚገባበት ሰነድ ነው” ይላል፡፡ ሦስተኛ ወገን ማለት ደግሞ “በመድን [ውሉ] መሰረት ኃላፊነት ያስከተለ የተሽከርካሪ አደጋ በደረሰ ጊዜ ከመድን ገቢው፣ ከመድን ገቢው ቤተሰብ፣ ከአሽከርካሪው ወይም ከመድን ገቢው ተቀጣሪ ሰራተኛ በስተቀር የመድን [ውሉ] ተፈፃሚነት የሚመለከተው ማንኛውም ሌላ ሰው ነው” ይላል፡፡ በመሆኑም የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ማለት የተሽከርካሪ አደጋ የደረሰበት ሰው ሊያገኘው የሚገባ ካሳ ወይም የሕክምና ወጪ ሽፋን መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን አስፈላጊነት
የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን አዋጅ ቁጥር 799/2005 እንሊወጣ ያስፈለገበት አራት ምክንያቶች በመግቢያው ላይ የተጠቀሱ ሲሆን እነዚህም በተሽከርካሪ ምክንያት እየደረሰ ያለው አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየጨመረ መምጣቱ፣ በተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት የሚደርሰው የሰው ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ኪሣራ ማህበራዊ ችግር እያስከተለ ያለ መሆኑ፣ የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት ማመቻቸት እና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን እዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ መድን ወይም ኢንሹራንስ እጅግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ከነዚህ ጠቀሜታዎቹ ውስጥ አንደኛው በአንድ ሰው ላይ የሚደርስን ፍትሐብሔራዊ ተጠያቂነትን፣ የንብረት ጉዳትን፣ በሞት ወይም የአካል ጉዳት ምክንያት የሚደርስን የኢኮኖሚያዊ ኪሳራን በካሳ መልክ የኢንሹራንስ ድርጅቱ ስለሚከፍለው በተቻለ መጠን ጉዳት አድራሽ ወይም ጉዳት የደረሰበት ሰው የከፋ ኪሳራና ምስቅልቅል ውስጥ እንዳይገቡ ያደርጋል፡፡
የሕጉ ተፈፃሚነት ወሰን
ህጉ ከብስክሌትና ከአካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪ (ዊልቼር) በስተቀር በመንገድ ላይ በሚሄድ በኤሌክትሪክ ወይም በመካኒካ ኃይል በሚሰራ ባለሞተር ተሽከርካሪ፣ ግማሽ ተሳቢ ወይም ተሳቢ ላይ ሁሉ ተፈፃሚ እንደሚሆን ከአዋጁ አንቀጽ 2(5) እና ከአንቀፅ 3 ጣምራ ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም ማለት ከባጃጅ እንስቶ ቀላልና ከባድ ተሽከርካሪዎች ሁሉ ይህን የመድን የምስክር ወረቀት ሳይዙ መንቀሳቀስ አይችሉም። በአዋጁ አንቀጽ 3(1) ላይ እንደተገለፀው ማንኛውም ሰው ተሽከርካሪው በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው አደጋ የፀና የመድን ሽፋን ሳይኖረው ተሽከርካሪውን በመንገድ ላይ መንዳት፣ መጠቀም ወይም ሌላ ሰው እንዲነዳ ወይም እንዲጠቀም ማድረግ ወይም መፍቀድ እንደማይችል ተደንግጎ እናገኛለን፡፡ የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ምስክር ወረቀት ካልያዙ ሽፋኑ እንደሌላቸው ተቆጥሮ ተሽከርካሪዎቹ በፖሊስ ተይዘው ይቆያሉ። ተሽከርካሪው የመድን ተለጣፊ ምልክት ከሌለው ወይም በወቅቱ የታደሰ ካልሆነ መድህን ለተሽከርካሪው የመግባት ግዴታ ያለበት ሰው አዋጁን እንደጣሰ ተቆጥሮ በሕግ እንደሚጠየቅ በአዋጁ አንቀጽ 13 ላይ ተደንግጓል። ለተሽከራካሪው የሦስተኛ ወገን መድን የመግባት ግዴታ ያለበት የተሽከርካሪው ባለቤት፣ ተሽከርካሪው ላይ በኪራይ ወይም በውክልና መብት አግኝቶ የሚጠቀም ሰው ወይም ሌሎች እንዲጠቀሙበት መፍቀድ የሚችል ማንኛውም ሰው ነው፡፡
የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን የሚሸፍነው ጉዳት
በአዋጁ አንቀጽ 4(2) ላይ በተገለፀው መሠረት የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ፖሊሲ መድን የተገባለት ተሽከርካሪ ለሚያደርሰው የሰው ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ኪሳራ መከፈል የሚገባውን ካሳና አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ወጪ የሚሸፍን ነው፡፡
ነገር ግን በመድን ገቢው ወይም ቤተሰብ (የትዳር ጓደኛ፣ ልጅ፣ አባት፣ እናት ወይም የሚያስተዳድረው ማንኛውም ሰው) ላይ የሚደርስ ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ጉዳት፣ በመድን ገቢው ተቀጥሮ የሚሰራ ሰው በሥራው ላይ እያለ በሚደርስ የግጭት አደጋ ወይም የሞት ወይም የአካል ጉዳት ወይም የንብረት ጉዳት፣ መድን በተገባለት ተሽከርካሪ ላይ የሚደርስ አደጋ፣ መድን በተገባለት ተሽከርካሪ ላይ በኪራይ ወይም በክፍያ በሚጓጓዝ ንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት ኃላፊነት እና ከኢትዮጵያ ግዛት ክልል ውጪ የደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ ተከትሎ የመጣ ኃላፊነትን የማይሸፍን መሆኑን እና ካሳ እንደማይከፈለው ከአዋጁ አንቀጽ 7 እንረዳለን፡፡ በሌሎች ሕጎች ግን ጉዳት አድራሹን ወይም ተሽከርካሪው የመድህን ሽፋን ካለው መድህን የሰጠውን ኩባንያ ካሳ የመጠየቅ መብታቸው እንደተጠበቀ ነው።
የካሳው መጠን
በአዋጁ አንቀጽ 16 መሰረት በሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪ መድን ፖሊሲ ለደረሰ ጉዳት የሚሸፍነው የካሳ መጠን የሞት አደጋ ከብር 5 ሺ ያላነሰና ብር 40 ሺ ያልበለጠ የገንዘብ ካሳ፣ በአንድ ሰው ላይ ለሚደርስ ለአካል ጉዳት ከብር 40 ሺ ያልበለጠ የገንዘብ ካሳ እንዲሁም በንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት ወይም ኪሳራ ከብር 100 ሺ ያልበለጠ የገንዘብ ካሳ የሚከፈል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሕግ ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን በላይ ጉዳት የደረሰበት ሰው ጉዳት አድራሹን ወይም በሕግ ኃላፊነት ያለበትን ሰው በፍ/ቤት ተገቢነት ባለው ሌላ ሕግ መሠረት ከሶ ካሳ መጠየቅ ይችላል፡፡
በሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪ የመድን ዋስትና የአሽከርካሪውን እድሜ፣ የአካል ወይም የአእምሮ ሁኔታ፣ የተሽከርካሪውን ሁኔታ፣ የፈረስ ጉልበት ወይም የሲሊንደር ችሎታ ወይም ዋጋ፣ የሚይዘው ሰው ብዛት፣ የሚጭነውን እቃ ክብደት፣ አካላዊ ባህሪ ወይም ልዩ መሳሪያ፣ ተሽከርካሪው አገልግሎት ላይ የሚውልበትን ጊዜ ወይም አካባቢ ካሳ እንዳይከፈል ገደብ ሊያስደርጉ አይችሉም።
እንዲሁም እንደ ሌሎች የመድን ዋስትናዎች በመድን ውሉ በተስማማነው መሠረት አይደለም በሚል የመድን ኩባንያው ወይም ሌላ አካል ካሳው እንዳይከፈል መቃወም ወይም መከልከል አይችልም። የመድን ፈንድ ኤጀንሲው ጉዳት አድራሹ ተሽከርካሪ ካልታወቀ ወይም የመድህን ሽፋን ከሌለው በተሽከርካሪው ለደረሰ የሞት ወይም የአካል ጉዳት ከላይ የጠቀስነውን የካሳ መጠን ይከፍላል። የአስቸኳይ ህክምና ወጪንም ይሸፍናል፡፡
አስቸኳይ የህክምና እርዳታ
ማንኛውም ሰው በተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት ከደረሰበት ከአደጋው ቦታ፣ ወደ ህክምና በሚጓጓዝበት ወቅትና በድንገተኛ ክፍል እስከ ብር 2 ሺህ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ የማግኘት መብት አለው፡፡ ማንኛውም የጤና ተቋም ይህን አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ክፍያ ሳይጠይቅ የመስጠት ግዴታ አለበት። ክፍያውን አገልግሎቱን ከሰጠ በኋላ ከመድን ኩባንያው ወይም ከመድህን ፈንድ ኤጀንሲው የሚጠይቅ መሆኑን በአዋጁ አንቀጽ 27(3) እና (4) ላይ ተገልጿል።
የመድን ምስክር ወረቀት እና ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ
የመድን ምስክር ወረቀት ማለት የተሽከርካሪው ባለንብረት ወይም ህጋዊ ግዴታ ያለበት ሰው ተሸከርካሪው በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው አደጋ በአዋጁ መሠረት መድን የገባለት መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰነድ ነው፡፡ መድን ሰጪ ድርጅት ከመድን ገቢው ጋር የመድን ሽፋን ለመስጠት ከተስማሙ የመድን ፖሊሲውን (የመድን ስምምነት ውላቸውን) ለመድን ገቢው ይሰጠዋል፡፡ ከመድን ፖሊሲው በተጨማሪ በአዋጁ አንቀጽ 9(1) እና 12(1) ላይ እንደተገለፀው የመድን ምስክር ወረቀት እና የመድን ተለጣፊ ምልክት ለመድን ገቢው አብሮ መስጠት እንዳለበት ሕጉ በመድን ድርጅቱ ላይ ግዴታ ጥሎበታል፡፡
ይህ በአዋጁ አንቀጽ 9 መሠረት የተሰጠ የመድን ምስክር ወረቀት ከተሰጠበት ቀን አንስቶ ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ የሚፀና ነው፡፡ የመድን ሽፋን ውሉ ሲቋረጥ ወይም የውል ዘመኑ ሲያልቅ መድን ገቢው የመድን ምስክር ወረቀቱንና የመድን ተለጣፊውን ወዲያውኑ ለመድን ሰጪው ድርጅት መመለስ አለበት፡፡
የመድን ፈንድ
የመድን ፈንድ ማለት ቋሚ የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ በኢትዮጲያ ብሔራዊ ባንክ በሚከፈት ልዩ የባንክ ሂሳብ ውስጥ ተቀማጭ እንዲሆን በአዋጁ የተቋቋመ ቋሚ የገንዘብ ምንጭ ነው፡፡ የፈንዱ የገንዘብ ምንጭ ከፈንዱ ተመን የሚሰበሰብ እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወሰን ሌላ ተጨማሪ ገቢ ነው፡፡ ይህን ፈንድ የሚስተዳደረው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በተቋቋመው የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ሲሆን የፌደራል መንግስት የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ስያሜው የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት በሚል ተቀይሯል፡፡
የፈንዱ ዓላማ መድን ባልተገባለት ወይም ባልታወቀ ተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ሰው አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ፣ የአካል ጉዳት ለደረሰበት ሰው ካሳ እንዲከፈለው ማድረግ እና ለሞተ ሰው ቤተሰብ አባላት ካሳ እንዲከፈል ማድረግ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 20(2) ላይ እንደተገለፀው ከፈንዱ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የሚከፍለው የካሳ ክፍያ መጠን መድን የተገባለት ተሽከርካሪ አደጋ ባደረሰ ጊዜ በሚከፈለው የካሳ መጠን ልክ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡
የመድን ፈንድ አገልግሎቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካላት በሕጉ የተቀመጠውን የጉዳት ካሳ መጠን ከከፈለ በኋላ ይህን የከፈለውን ክፍያ ለጉዳቱ በኃላፊነት ተጠያቂ ከሆነው ሰው ላይ የማስመለስ መብት እንዳለው በአዋጁ አንቀጽ 20(3) ተደንግጎል፡፡
ተጠያቂነት
የተሽከርካሪ የሶስተኛ ወገን ህግን አለማክበር የማስተካከያ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ከማስከተሉም በተጨማሪ ክልከላዎችን ተላልፎ መገኘት ከብር 3 ሺ እስ ብር 5 ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከ1 አመት እስከ 2 አመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ በአዋጁ አንቀፅ 30 ተደንግጓል፡፡
የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ህግ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ከደረሰባቸው ችግር በተወሰነ መልኩ እንዲቋቋሙ እና አስቸኳይ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ለማስቻል ተግባራዊ የተደረገ ህግ ነው፡፡ ስለሆነም ሕብረተሰቡም የተሽከርካሪ አደጋ እንዳይደርስ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ አደጋ ከደረሰ ግን በጠቀስናቸው መብቶች መጠቀም የሚችል መሆኑን መገንዘብ እንዳለበት መጠቆም እንወዳለን፡፡
መረጃው፡- የኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር
ለተጨማሪ መረጃዎች፡-
የፌስቡክ ገጻችን https://www.facebook.com/jlrti
የቴሌግራም ገጻችን https://t.me/jlrtinet ይቀላቀሉ!

ሰዎች በእለት ተእለት በሚኖራቸው መስተጋብር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በራሳቸው መፍታት ሳይችሉ ሲቀሩ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ማቅረባቸው በየእለቱ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ ፍርድ ቤት ሲቀርብም ከክስ አቀራረብ ጀምሮ የክርክር ሂደቱ የሚመራበት ሥነ ሥርአት አለው፡፡ በዚህ አጭር ፅሁፍ አንድ ሰው የፍትሐብሔር ክስ ቀርቦበት መልስ በሚያቀርብበት ወቅት ሊቀርብ የሚችልን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ምንነት እንዲሁም የሚቀርብበት ጊዜና ሁኔታ እንመለከታለን።

የመጀመሪያ ደርጃ መቃወሚያ ምንነት
የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ማለት ወደ ዋናው ክርክር መግባት ሳያስፈልግ የቀረበው ክስ ውድቅ የሚሆንበትን ምክንያት በመግለፅ ክሱ ውድቅ እንዲሆን በማንኛውም ተከራካሪ ወገን የሚቀርብ መቃወሚያ እንደሆነ ከፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህግ ቁጥር 244(1) መረዳት ይቻላል።
የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ምክንያቶች
አንድ ሰው የፍትሐብሔር ክስ ቀርቦበት መልስ እንዲያቀርብ በታዘዘ ጊዜ በቀረበበትን ክስ ላይ ከሚያቀርባቸው ክርክሮች መካከል አንዱ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ነው። የፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህግ ቁጥር 244(2) የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ሊቀርብ የሚችልባቸውን ምክንያቶች በዝርዝር አመልክቷል፡፡ ይኸውም፡-
  1. ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤት ነገሩን ወይም የቀረበውን ክስ ለመስማት ስልጣን የሌላው ከሆነ
  2. ክስ የቀረበበት ጉዳይ አስቀድሞ በፍርድ የተወሰነ ጉዳይ ከሆነ
  3. ክስ የቀረበበት ጉዳይ በሌላ ፍርድ ቤት ቀርቦ በክርክር ላይ ያለ ከሆነ
  4. አንደኛው ተከራካሪ ወገን በነገሩ የማያገባው መሆኑን በመግለፅ በጉዳዩ ገብቶ መከራከር አይገባውም የሚባል ከሆነ
  5. ክሱ በይርጋ የታገደ ከሆነ
  6. ክሱ የተነሳበት ነገር በሽምግልና ታይቶ በስምምነት የተፈፀመ ወይም ለእርቅ የተቀጠረ ከሆነ ይህን በመግለፅ መቃወሚያ ሊቀርብ ይችላል።
ለቀረበበት ክስ መልስ የሚሰጥ ማንኛውም ወገን ከላይ ከተጠቀሱት መቃወሚያዎች አንዱን ወይም ከአንድ በላይ እንደመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ሊያቀርብ የሚችል ሲሆን በተቻለ መጠን በቶሎ ተጠቃለው መቅረብ አለባቸው። አንድ ተከራካሪ መቅረብ ከሚገባው መቃወሚያ ውስጥ አንዱን የተወ እንደሆነ ፍርድ ለመስጠት የሚያሰናክል ካልሆነ በስተቀር መቃወሚያውን ለማቅረብ እንዳልፈለገ እንደሚቆጠር በድንጋጌው ንኡስ ቁጥር 3 ላይ በግልፅ ተመልክቶ ይገኛል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ በፍርድ ቤት የሚሰጥ ውሳኔና ውጤቱ
የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ሲቀርብ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ ሌላኛው ወገን በጉዳዩ ላይ ያቀረበውን ክርክር ከሰማ በኋላ በቀረበው መቃወሚያ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ማስረጃ እንዲቀርብለት በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህግ ቁጥር 245(1) መሰረት ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል። የቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ተገቢና በቂ በሆነ ማስረጃ የተደገፈ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ባረጋገጠ ጊዜ የቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ክስ የቀረበበት ጉዳይ አስቀድሞ በፍርድ የተወሰነ ጉዳይ በመሆኑ ወይም ክሱ የተነሳበት ነገር በሽምግልና ታይቶ በስምምነት የተፈፀመ በመሆኑ ወይም ለእርቅ የተቀጠረ በመሆኑ እንደሆነ የቀረበውን ክስ በመዝጋት ባለጉዳዮችን ያሰናብታል። የቀረበው መቃወሚያ ከእነዚህ ውጭ ሆኖ መቃወሚያው ተገቢ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ባረጋገጠ ጊዜ መዝገቡን በመዝጋት ተገቢ መስሎ የታየውን ትእዛዝ ይሰጣል።
ሌላው የቀረበው መቃወሚያ ተቀባይነት አግኝቶ መዝገቡ የተዘጋ እንደሆነ ከሳሽ ክሱን አሻሽሎ በዚያው ጉዳይ መጀመሪያ ክስ ላቀረበበት ፍርድ ቤትም ይሁን ለሌላ ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ክሱን እንደገና የማቅረብ መብቱ የተረጋገጠ ሲሆን ፍርድ ቤቱም መዝገቡን በሚዘጋበት ወቅት ከሳሽ እንደገና ክስ የማቅረብ መብት እንዳለው በትእዛዙ ላይ መግለፅ እንደሚችል በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህግ ቁጥር 245(3) ላይ በግልፅ ተደንግጎ ይገኛል።
በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ መዝገቡን የዘጋው ‘ፍርድ ቤቱ ነገሩን የማየት ስልጣን የለውም’ በሚል መቃወሚያ መሰረት ሲሆን ከሳሽ ከከፈለው የዳኝነት ገንዘብ ላይ የሚቀነሰው ተቀንሶ የተረፈው ገንዘብ እንደሚመለስለት በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህግ ቁጥር 245(4) ላይ በግልፅ ተደንግጓል። በአጠቃላይ የፍትሐብሔር ክስ የቀረበበት ማንኛውም ሰው ወደ ዋናው ክርክር ከመግባቱ በፊት በፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህግ ቁጥር 244 ሥረ የተዘረዘሩት ምክንያቶች ባሉ ጊዜ ይህንኑ በመጥቀስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ማቅረብ የሚችል ሲሆን ይህም ወዲያውኑ መቅረብ ያለበት መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃዎች የጤሌግራም ቻናላችንን ይወዳጁ! https://t.me/jlrtinet

መረጃው፡- የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ነው!

በተለያዩ አጋጣሚዎች ኤግዚሂቢት ተያዘ፣ ኤግዚቢት ተመለሰ፣ ቀረበ ወዘተ ሲባል ሰምተዋል ብለን እናስባለን። ለመሆኑ ኤግዚቢት ምንድን ነው?
በክርክር ሂደት የአንድን አከራካሪ ፍሬ-ነገር መኖር ወይም አለመኖር ማረጋገጥ የሚቻለዉ ማስረጃ በማቅረብ ነዉ፡፡ ማስረጃ በምስክሮች፣ በሰነድ ወይም በተለይ በወንጀል ክርክር በኤግዚቢት መልክ ሊቀርብ ይችላል፡፡ በዚህ ፅሁፍ የኤግዚቢትን ምንነት እና ኤግዚቢትን በሚመለከት የሚሰጡ ውሳኔዎችን በአጭሩ እንደመለከታለን፡፡

የኤግዚቢት ምንነት
ኤግዚቢት በወንጀል ምርመራ ወይም ክስ ሂደት አንድን ፍሬ ነገር ለማረጋገጥ ማስረጃ ተደርጎ የሚቀርብ ተጨባጭነት ያለው ንብረት ወይም ቁስ (real item) ነው፡፡ አንድ ቁስ ኤግዚቢት ሊሆን የሚችለው ተፈፀመ ከተባለው የወንጀል ድርጊት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አሣማኝ ግንኙነት ያለው ሲሆን ነው፡፡ ኤግዚቢት ወንጀሉ የተፈፀመበት፣ ለመፈፀሚያነት የዋለ እና ሌላ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያለውን ቁስ ሁሉ ያካትታል፡፡
ኤግዚቢትን በተመለከተ የሚሰጡ ውሳኔዎች
ዐቃቤ ህግ ኤግዚቢቱ የማስረጃነት ጠቀሜታ ያለው ሆኖ ካገኘው ክስ ሲመሰርት የኤግዚቢቱን ምንነት እና ያለበትን ሁኔታ በማስረጃ ዝርዝር በመጠቀስ ሊጠቀምበት ወይም ፍርድ ቤት ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ኤግዚቢት በዚህ መልኩ በማስረጃነት የሚቀርበው ፍርድ ቤት ተመልክቶት በክሱ የተካተተው የወንጀል ፍሬ ነገር መፈፀሙን ግንዛቤ እንዲወስድ ለማስቻል ሲሆን ፍርድ ቤቱ በዋናው ጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሲሰጥ አብሮ ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል፡፡ በአንፃሩ ዐቃቤ ህግ የቀረበውን ኤግዚቢት የማስረጃነት ጠቀሜታ ካላገኘበት ወይም ሌላ በቂ ማስረጃ ካለው እንደ ኢግዚቢቱ አይነት ንብረቱ ለባለቤቱ እንዲመለስ፣ በህግ መሰረት ለመንግስት ገቢ መሆን ያለበት ከሆነ ገቢ እንዲሆን ወይም አደገኛ በመሆኑ መወገድ ያለበት ከሆነ እንዲወገድ ሊወስን ይችላል፡፡
ፍርድ ቤት ኤግዚቢት በማስረጃነት ተጠቅሶ ከቀረበለት ኤግዚቢቱ ለወንጀል ተግባር ሊያገለግል የሚችል ወይም ያገለገለ ወይም የወንጀል ተግባር ፍሬ ከሆነ እና የህዝብ ሰላም፣ ጤና እና መልካም ጠባይን የሚጎዳ ሲሆን እንዲወረስ የመወሰን ስልጣን አለው፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 100(1) መሰረት ወንጀል ለመፈፀም ማነሳሻ፣ ለተፈፀመ ወንጀል ዋጋ የተሰጠ ወይም ሊሰጥ የታቀደ ጥቅም ሁሉ ለመንግስት ገቢ ይሆናል፡፡ በወንጀል ህግ አንቀፅ 98(2) ላይ እንደተመለከተው ተከሳሹ ጥፋተኛ ከተባለ ወንጀለኛው በወንጀል ተግባሩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያገኘውን ንብረት ሁሉ እንዲወረስ ሊወሰን ይችላል፡፡ በአንፃሩ ንብረቱ የግለሰብ ንብረት ከሆነ እና ንብረቱ አደገኛነት የሌለው ወይም በህግ ያልተከለከለ የንፁ ሶስተኛ ወገኖች ንብረት ከሆነ ለባለቤቱ እንደሚመለስ ከወንጀል ህጉ አንቀፅ 140(2) መረዳት ይቻላል፡፡ ሆኖም ባለንብረቱ እስከ 5 አመት ካልተገኘ ለመንግስት ገቢ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ንብረቱ በባህሪው ጎጂ ከሆነ ማለትም እንደ አደገኛ እፅ፣ የተበላሹ መድሀኒቶች እና የመሳሰሉት ከሆነ እንዲወገድ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
በሌላ መልኩ የሚነሳው እግዚቢት እና የወንጀል ፍሬ መካከል ያለው ግንኘነት ነው፡፡ እላይ በተገለፀው አግባብ አንድ ማስረጃ ኤግዚቢትም የወንጀል ፍሬም ሊሆን ይችላል፡፡ አግዚቢት የወንጀል ፍሬ በሚሆንበት ጊዜም በህግ የሚወረስ ሲሆን ይህንኑ እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ህጋዊ ለማስመሰል መሞከር በተጨማሪ ወንጀል ያስጠይቃል፡፡ በዚህም በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኘነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀፅ 35 መሰረት ንብረቱ ወይም ገንዘቡ ከወንጀል የተገኘ ሲሆን ህጋዊ ለማስመሰል ከተሞከረ ለወንጀሉ መፈፀሚያ የዋለ ንብረት፣ በንብረቱ ተለውጦ የተገኘው ፍሬ፣ ንብረቱ ተቀላቅሎት የተገኘው ወንጀለኛው ንብረት እንደሚወረስ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የሙስና ወንጀልን በተመለከተ በተሻሻለው ልዩ የፀረ ሙስና ሥነ ሥርአትና የማስረጃ ህግ አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀፅ 29 መሰረት በሙስና ወንጀሉ ወንጀለኛው ያገኘው ንብረት እና በዚሁ ንብረት ያፈራው ንብረት እንዲሁም በመንግስት፣ በህዝባዊ ድርጅት እና የመንግስት የልማት ድርጀት ጥቅም ላይ ላደረሰው ጉዳት ማካካሻ የሚሆን የወንጀለኛው ንብረት ሊወረስ ይችላል፡፡
በጥቅሉ ኤግዚቢት ከአንድ ከተፈፀመ ወንጀል ጋር ግንኙነት ያለው እና ወንጀሉ ስለመፈፀሙ የሚያሳይ ተጨባጭነት ያለው ንብረት ወይም ቁስ ሲሆን ይህንኑ ንብረት በተመለከተ የሚሰጡ ውሳኔዎችም እንደየጉዳዩ አይነት ንብረቱ በመንግስት እንዲወረስ፣ ለባለቤቱ እንዲመለስ ወይም እንዲወገድ ሊወሰን ይችላል፡፡
ለተጨማሪ መረጃዎች የቴሌግራም ቻናላችንን ይወዳጁ! https://t.me/jlrtinet

መረጃው፡- የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ነው!

አጫጭር መጣጥፎች

ዘመናዊ የመታወቂያ ስርዓት በአንድ ሀገር ውስጥ ተግባራዊ ሲደረግ መሰረታዊ የሚባሉ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፣ ከነዚህ ጠቀሜታዎች መካከልም ሃገራዊ ልማትን በአግባቡ ለማቀድ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ሽግግር ለመፍጠር፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የሀብት ብክነትን ለመቀነስ፣ ወንጀልን ለመከላከል፣ ፖሊሲዎች ሲቀረጹ እና የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ድግግሞሽን ለመቅረፍ እና አካታችነትን ለማጎልበት የሚረዳ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ በኢትዮጵያም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የበለፀገ፣ ዘርፍ ተሻጋሪ፣ መሠረታዊ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መዘርጋት አሰፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ተቋቁሞ ላለፉት ሁለት ዓመታት በግንባታና በሙከራ ሂደት ላይ ቆይቷል። በዚህ ሂደት ውስጥ ከተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ጋር ለማስተሳሰር የሙከራ ትግበራ ስራዎችን በማከናወን ወደ 1.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎችን መዝግቦ አብዛኞቹን የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ ተችሏል።
በዚህ የሙከራ ትግበራ ወቅት ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ ሌላው የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ማዘጋጀት ሲሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ "የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 1284/2015" አድርጎ አፅድቆታል፡፡ አዋጁ ከሌሎች ሀገሮች የመታወቂያ አዋጆች አንፃር ዘግየት ብሎ የወጣ በመሆኑ በሌሎች ሀገሮች የታዩ ክፍተቶችን ለመድፈን በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ዘመኑ የደረሰበትን የዲጂታል መታወቂያ በዘመናዊ መልኩ ለነዋሪዎች ለመስጠት እና ለማስተዳደር በማለም የወጣ ነው፡፡ አዋጁ በርካታ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን፣ በዝርዝር በሌላ ፅሁፍ የምንመለስበት ሲሆን፣ በዚህ ክፍል የአዋጁን ዋናዋና ድንጋጌዎች በተለይም ከዓላማዉ ጋር በማገናኘት ለማየት እንሞክራለን፡፡

1. የዲጂታል መታወቂያ ምንነት እና አገልግሎት
በየትኛውም ሀገር የሚገኝ የመታወቂያ ሥርዓት በሁለት የሚከፈል ሲሆን እነሱም አገልግሎት ተኮር መታወቂያ (Functional ID) እና መሰረታዊ መታወቂያ (Foundational ID) ናቸው፡፡ አገልግሎት ተኮር የመታወቂያ (Functional ID) ማለት የተወሰነ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል መታወቂያ ነው። እንዲህ አይነት መታወቂያ፣ ከተሰጠበት አገልግሎት ውጭ ለሌሎች ነዋሪነትን እና ማንነትን በማረጋገጥ ለሚሰጡ አገልግሎቶች ተቀባይነት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ መሰረታዊ መታወቂያ (Foundational ID) ማለት በተሰጠበት ሀገር ውስጥ በየትኛውም ቦታ ተቀባይነት ያለው እና ማንነትን በማረጋገጥ ለሚሰጡ የትኛውም አገልግሎቶች ተቀባይነት ያለው የመታወቂያ አይነት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መሰረታዊ መታወቂያ (Foundational ID) ለአገልግሎት ተኮር መታወቂያዎች (Functional ID) እንደመረጃ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡
መሰረታዊ መታወቂያ በተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ስያሜዎች ሊኖሩት የሚችሉ ሲሆን ብሄራዊ መታወቂያ ወይም የዲጂታል መታወቂያ በብዛት መሰረታዊ መታወቂያ የሚጠራባቸው ስያሜዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት ተግባራዊ ለማድረግ በሙከራ ላይ የሚገኘው የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት (Foundational ID) መሰረታዊ መታወቂያ የሚሰጥበት ስርዓት ነው፡፡ የዲጂታል መታወቂ ማለት ማንኛውም በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖር ሰው ተቋሙ ወይም በተቋሙ ውክልና የተሰጠው አካል በሚያደርገው የምዝገባ ሂደት የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ መረጃዎችን በመስጠት ከተመዘገበ በኋላ ማንነቱን ለማረጋገጥ የሚሰጥ ልዩ ቁጥር(Unique Number) ነው፡፡ ይህ ልዩ ቁጥር ወይም ዲጂታል መታወቂ የሚመነጨው ከግለሰቡ የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ ዳታ በመሆኑ፣ ግለሰብን በልዩ ሁኔታ ለመለየት የሚስያስችል አስተማማኝ የመታወቂ ስርዓት ነው፡፡
ይህን የመታወቂያ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እና የህግ ድጋፍ እንዲኖረው ለማስቻል በብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ከተዘጋጀ በኋላ ረቂቁን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 1284/2015 አድርጎ አፅድቆታል፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 14 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው የዲጂታል መታወቂያ የአንድን ነዋሪ ማንነትን ለማስረዳት ወይም ለማረጋገጥ እንደ ህጋዊ እና በቂ ማስረጃ ተደርጎ እንደሚወሰድ እና ማንኛውም ተጠቃሚ አካል ለነዋሪው ለሚሰጠው አገልግሎት የዲጂታል መታወቂያ እንደ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ የሚያደርግ አሠራር በሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል ፍቃድ መዘርጋት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም አሁን በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚደረገው ዲጂታል መታወቂያ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተቀባይነት ያለው እና ማንነትን በማረጋገጥ ለሚሰጡ አገልግሎቶች እንደ አስገዳጅ የመታወቂያ አይነት የሚወሰድ ሲሆን፣ በዚህ መታወቂያ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው በወንጀል እንደሚጠየቅ አዋጁ አንቀፅ 21/1/ በሚከተለው መልኩ ደንግጓል፡፡
"በዚህ አዋጅ እና ይህን አዋጅ ተከትለው በሚወጡ ደንቦች እና መመሪያዎች መሠረት ስልጣን ባለው አካል የተሰጠን ዲጂታል መታወቂያን እንደ ህጋዊ መታወቂያ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነ ወይም ማንነትን ብቻ በማረጋገጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆነ ወይም በዚህ አዋጅ አንቀፀ 19 ላይ የተመለከተውን የመተባበር ግዴታ የተላለፈ ማንኛውም ሰው ከአስር ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል" ከላይ እንደተገለጸው ዲጂታል መታወቂያ የሚባሉው ልዩ ቁጥሩ ሲሆን፣ ይህንን መታወቂያ በካርድ መልኩ መያዝ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ተገቢውም ክፍያ በመፈፀም ከተቋሙ ወይም ተቋሙ ውክልና ከሰጠው ማንኛውም አታሚ ድርጅት የመታወቂያ ካርዱን ማግኘት የሚቻልበት ስርዓት ተዘርግቷል፡፡
2. የአዋጁ ዓላማ
የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 1284/2015 ዋና ዓላማው የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ምንድን ነው የሚለው ሰፊ ትንታኔ የሚፈልግ ሲሆን፣ ጠቅላላ የሆነ ትርጓሜውን ግን ከዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ዓላማ ከሚለው ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በመሆኑም በአዋጁ አንቀፅ 5 ላይ እንደተመለከተው የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ዓላማ ነዋሪዎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ሲንቀሳቀሱ በቀላሉ የመታወቅ መብታቸው እንዲረጋገጥ በማድረግ ለሰብአዊ መብቶቸ አከባበር እና ለመልካም አስተዳደር መሻሻል አስተዋፅኦ ማድረግ፣ አገልግሎት ማግኘት የሚፈልጉ ግለሰቦችን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት በመዘርጋት በአገልግሎት ሰጪ እና አገልግሎት ተቀባይ መካከል እምነት እንዲጎለብት ማድረግ፣ ሕገ-ወጥ ተግባራትን መከላከል፣ ሀገር አቀፍ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት በማደራጀት ሀገራዊ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና እቅዶች ሲቀረጹ እና የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ድግግሞሽን መቅረፍ፣ በዚህም የሀብት ብክነትን መቀነስ እና አካታችነትን ማጎልበት፣ የነዋሪዎችን የዲሞግራፊክ እና ባዮሜትሪክ መረጃ ለመሰብሰብ የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት፣ ለሌሎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ላልሆኑ አካላት የመታወቂያ ሥርዓት መረጃ ምንጭ ሆኖ ማገልገል እና አገልግሎት ተኮር የሆኑ የመታወቂያ ሥርዓቶች ወደ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት እንዲሸጋገሩ ማጠናከር መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተርም በአንቀጽ 6 ላይ ″ማንኛውም ሰው ነፃነቱና አካላዊ ደህንነቱ ተጠብቆለት የመኖር መብት አለው፡፡ ቀድሞ በሕግ በተደነገጉት ሁኔታዎችና ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ነፃነቱን እንዲያጣ ሊደረግ አይችልም" በማለት ደንግጓል፡፡
3. የዲጂታል መታወቂያ የማግኘት መብት እና ዲጂታል መታወቂያ ለማግኘት ስለሚሰበሰቡ መረጃዎች
በአዋጁ አንቀፅ 7 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ሰው የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ መረጃዎችን በመስጠትና በመመዝገብ የዲጂታል መታወቂያ የማግኘት መብት አለው፡፡ ነዋሪው የዲጂታል መታወቂያ ለመውሰድ እሱነቱን ለማረጋገጥ የሚያገለግሉ የመታወቂያ ሰነዶች እና ሌሎች በተቋሙ ተቀባይነት ያላቸውን ሰነዶች ወይም የሰው ምስክር ማስረጃዎችን በመጠቀም በማረጋገጥ መመዝገብ ይችላል፡፡ ከላይ እንደተመለከተው ወደ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት የሚገባ የግል መረጃ የእያንዳንዱን ተመዝጋቢ የዲሞግራፊክ መረጃ እና ባዮሜትሪክ መረጃን ያካተተ መሆን ያለበት ሲሆን፣ የዲሞግራክ መረጃ የሚባሉትም ስም ፣ የአባት ስም ፣ የአያት ስም ፣ ወይም በዚህ መልክ የተደራጀ ህጋዊ ስም ለሌለው ተመዝጋቢ ተቋሙ ህጋዊ የሆነውን ስያሜ ወይም ተመዝጋቢው በአካባቢው ማህበረሰብ የሚጠራበትን ስም፣ ዜግነት፣ የትውልድ ቀን፣ ወር እና ዓመት፣ ፆታ፣ መኖሪያ አድራሻ ሲሆኑ እንደአስፈላጊነቱ ስልክ ቁጥር፣ የኢሜይል አድራሻ እና ፖስታ አድራሻንም ሊያካትት ይችላል፡፡ የሚሰበሰቡት የባዮሜትሪክ መረጃዎች ድግሞ የአስር ጣት አሻራ፣ የሁለቱም አይኖች ብሌን እና የፊት ገፅታ ናቸው፡፡ እነዚህን የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ መረጃዎች የሰጠ ማንኛውም ሰው የዲጂታል መታወቂያ ማግኘት ይችላል፡፡
አንዳንድ ጊዜ የባዮሜትሪክ መረጃዎችን ለመስጠት የሚቸገሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ጣት የሌለው ሰው፣ በእርጅና እና በተለያዩ ምክንያቶች አሻራቸው የማይነበብ ሰዎች በሚኖሩበት ጊዜ እና መሰል ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ፣ በዲሞግራፊክ መረጃ ብቻ መታወቂያውን መስጠት የሚገባ ስለመሆኑ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
4. የዲጂታል መታወቂያ ከሌሎች መታወቂያዎች፣
የባንክ አካውንቶች እና መሰል ማንነትን ለማረጋገጥ ከሚያገለግሉ ሰነዶች ጋር የሚኖረው ግንኙነት የዲጂታል መታወቂያ ራሱን የቻለ መታወቂያ ቢሆንም፣ ሌሎች መታወቂያዎችን የሚያጠናክር የመታወቂያ አይነት ነው፡፡ ሁሉም ከላይ በርዕሱ ላይ የተመለከቱን ማንነትን ለማረጋገጥ የሚያገለግሉ ሰነዶች ወደ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት እንዲገቡ የሚደርግ አሰራር ተዘርግቷል፡፡ ለምሳሌ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤቱ ከብሄራዊ ባንክ ጋር በመተባበር ከሁሉም በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ባንኮች ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ፣ ሁሉም ባንኮች ደንበኞቻቸውን ወደ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ለማስገባት ስራ ጀምረዋል፡፡ እንዲሁም ፅህፈት ቤቱ እና ገቢዎች ሚኒስቴር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ሁሉንም ግብር ከፋይ የታክስ ከፋይነት መለያ ቁጥሩን መሰረት በማድረግ ወደ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ለማስገባት የሚስችል ስራ ተጀምሯል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የምንችለው የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ሌሎች መታወቂያ ስርዓቶችን እያጠናከረ የሚሄድ የመታወቂያ አይነት መሆኑን እና ራሱንም ችሎ ማናቸውንም አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል የመታወቂያ አይነት መሆኑን ነው፡፡
5. የመረጃ አጠባበቅ ስርዓት
የዲጂታል መታወቂያ ለማግኘት የሚሰበሰቡ መረጃዎች በተለይም የባዮሜትሪክ መረጃዎች በጥንቃቄ ካልተያዙ ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሊያጋልጡ ይችላሉ፡ ስለዚህ ለዲጂታል መታወቂያ የተሰበሰቡ መረጃዎች በጥንቃቄ መያዝ ያለባቸው በመሆኑ አዋጁ ተቋሙ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት የግል መረጃን በአስተማማኝነት የሚይዝ ጠንካራ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት አለበት፤ በሚል የደነገገ ሲሆን፣ አሰራርና ህግን ጠብቆ በዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ለተሰበሰበ የማንኛውም ተመዝጋቢ ግላዊ መረጃ ያለ ተመዝጋቢው ፈቃድ ለሌላ ሰው መግለጽ ፣ ማስተላለፍም ሆነ እንዲለወጥ መፍቀድ የተከለከለ መሆኑን ህጉ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ይህን ክልከላ መተላለፍም በወንጀል የሚስጠይቅ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጥፅ 25 ላይ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ለፍትህ ስራ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በህግ ስልጣን ለተሰጠው ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት የግል መረጃው ለሚመለከተው ህጋዊ አካል ሊገለጽ ወይም ሊተላለፍ እንደሚችል የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 1284/2015 አንቀፅ 16 ተደንግጓል፡፡
የቴሌግራም ቻናል ቤተሠቦቻችን ቁጥር1K ደርሷል!! እርስዎም ይቀላቀሉና ወዳጅነታችንን በማጠናከር አዲስና አሥተማሪ መ ረጃዎችን ያግኙ!!
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ! https://t.me/jlrtinet ሙሉ መረጃ ለማዉረድ

አጫጭር መጣጥፎች

በወንጀል ህጉ አንቀፅ 682 መሰረት መሸሸግ ማለት ዕቃው የተገኘው በአንድ ንብረት ላይ በተፈፀመ ወንጀል ምክንያት መሆኑን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባ ይህንኑ ዕቃ በመግዛትም ሆነ በተውሶ፣ በስጦታ፣ በመያዣነት መቀበል ወይም በማናቸውም ይህን በመሳሰለ አኳኋን መውሰድ፣ መገልገል፣ ማስቀመጥ ወይም መደበቅ፣ አሳልፎ መሸጥ ወይም በመሸጥና በመለወጥ ስምምነት ውስጥ አገናኝ በመሆን መርዳት እንዲሁም የወንጀል ተግባር ባስገኘው ፍሬ የመጣ መሆኑን እያወቁ በዚሁ በወንጀል ድርጊት በተገኘ ዕቃ ምትክ በልዋጭ የተገኘውን ወይም በሽያጭ ዋጋ የተገዛውን ሌላ አይነት ነገር ወይም ጥሬ ገንዘብ መቀበል ነው፡፡ በዚህ መሰረት የመሸሸግ ወንጀል ተፈፅሟል ለማለት

  1. ተሸሽጎ የተገኘው ዕቃ በአንድ ንብረት ላይ በተፈፀመ ወንጀል ምክንያት የተገኘ ወይም የወንጀሉ ተግባር ባስገኘው ፍሬ የመጣ መሆን
  2. ሸሻጊው ዕቃው በወንጀል ምክንያት መገኘቱን ማወቅ ወይም መገመት ሲገባው በቸልተኝነት ወንጀሉን የፈፀመ መሆን
  3. በወንጀል ተግባር የተገኘን ዕቃ የገዛ፣ የተቀበለ፣ የወሰደ፣ የተገለገለ ወይም በመሰል ድርጊት ውስጥ የተገኘ መሆን አለበት፡፡
የመሸሸግ ወንጀል የህግ ተጠያቂነት
ከላይ በተገለፀው ሁኔታ የመሸሸግ ወንጀል አስቦ የፈፀመ ማንም ሰው በቀላል እስራት ወይም ከባድ በሆነ ጊዜ ከአምስት አመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡ ድርጊቱ በቸልተኝነት የተፈፀመ እንደሆነ ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡
ከባድ መሸሸግ
የመሸሸግ ወንጀል የተፈፀመው
  1. በሰዎች ወይም በንብረት ላይ ወንጀል ለመፈፀም የተቋቋመ ቡድን አባልነት እንደሆነ
  2. ወንጀል ፈፃሚው የተሰጠውን የሥራ ወይም የንግድ ፍቃድ በወንጀል የተገኘን ንብረት ለመሸሸግ ተገልግሎበት እንደሆነ
  3. ወንጀል ፈፃሚው የሸሸገው ንብረት የውንብድና፣ የዘረፋ፣ የባህር ውንብድና፣ የቅሚያ፣ የማስፈራራት ፍሬ መሆኑን ወይም ዕቃው የተገኘው
  4. ከመከላከያ ሠራዊት ንብረት ወይም በጠቅላላው ከመንግስት ሀብት ውስጥ መሆኑን እያወቀ እንደሆነ ወንጀሉ ከባድ የመሸሸግ ወንጀል የሚሆን ሲሆን ፈፃሚውም አስራ አምስት አመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና እስከ ብር ሀያ ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ህብረተሰቡ በማወቅም ወይም በቸልተኝነት በእንድ የወንጀል ድርጊት አማካኝነት የተገኘን ንብረት መግዛት፣ መዋስ፣ በስጦታ ወይም በመያዣነት መቀበል ወዘተ በወንጀል የሚያስቀጣ መሆኑን በመገንዘብ ዕቃዎች ሲገዛም ሆነ በተለያዩ መንገዶች ሲቀበል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

የቴሌግራም ቻናል ቤተሠቦቻችን ቁጥር1K ደርሷል!! እርስዎም ይቀላቀሉና ወዳጅነታችንን በማጠናከር አዲስና አሥተማሪ መረጃዎችን ያግኙ!!
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ! https://t.me/jlrtinet
Ministry of Justice/ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ሙሉ መረጃ ለማዉረድ

አጫጭር መጣጥፎች

ሰዎች በማህበራዊ መስተጋብር እርስ በርሳቸው በሚኖራቸው ግንኙነት ህጋዊ ተግባራትን ለመፈፀም፣ መብታቸውን ለማስከበር፣ ግዴታቸውን ለመወጣት እንዲሁም ህጋዊ ሀላፊነት ወይም ተጠያቂነትን ለመውሰድ ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል። በ1960 እ.ኢ.አ በወጣው የኢትዮጵያ ፍሐሀብሔር ህግ እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ችሎታ የሌለው መሆኑ በሕግ ተወስኖ ካልተገለፀ በቀር ማንኛውንም ዓይነት የማህበራዊ ኑሮውን ተግባር ለመፈፀም ችሎታ አለው። ይህም የሚያሳየው ህግ የሚወስደው ግምት ማንኛውም ሰው በመርህ ደረጃ ችሎታ እንዳለው ነው። በዚህ አጭር የንቃተ-ህግ ፅሁፍ የሰዎች ችሎታ ምንነት፣ የችሎታ ጠቀሜታ ወይም አስፈላጊነት እንዲሁም የሰዎች ችሎታ የማይኖርባቸውን ሁኔታዎች ከፍሐሀብሔር ህጉ አንፃር እንዳስሳለን።

የሰዎች ችሎታ ምንነት
የህግ መዝገበ ቃላት በሆነው መሪያም ዌብስተር እንደተሰጠው ትርጉም ህጋዊ ችሎታ ማለት አንድ ሰው በሕግ መሠረት አንድን የተወሰነ ሁኔታ ወይም ግንኙነት ከሌላው ጋር የማድረግ ወይም በአንድ የተወሰነ ሥራ ወይም ግብይት ላይ የመሳተፍ ችሎታ እና ኃይል ነው። በተጨማሪም ችሎታ ውሳኔ ለማድረግ መረጃን የመጠቀም እና የመረዳት ችሎታ እና ማንኛውንም ውሳኔ ማስተላለፍ አቅም ማለት ነው። አንድ ሰው አእምሮው ከተዳከመ ወይም በሆነ መንገድ ጤናው ከተጓደለ አቅም ይጎድለዋል። ይህም ማለት በዚያን ጊዜ ውሳኔ ማድረግ አይችልም ማለት ነው። የሕግ ችሎታ በሕጉ መሠረት በእኩልነት የመስተናገድ መሠረታዊ የሰብአዊ መብት አካል ነው። በመሆኑም ችሎታ ያለው ሰው በፍትሐብሔር ሥነ ስርዓት ህግ ቁጥር 33(1) መሰረት ፍትሐብሔር ክስ ማቅረብ የሚችል ሲሆን የፈፀመው የወንጀል ድርጊትም ካለ የወንጀል ህጉ መሰረት ሀላፊነት ይሆናል ማለት ነው።
የችሎታ ጠቀሜታ ወይም አስፈላጊነት
ችሎታ ህጋዊ ግንኙነቶችን በራስ ለማከናወን ጠቀሜታ አለው። ለአብነት ያክል አንድ ሰው ውል በራሱ ለመዋዋል ለምሳሌ ሽያጭ ለመፈፀም ችሎታ ሊኖረው ይገባል። ይኸውም እድሜው በህግ በተወሰነው ልክ መሆን ያለበት እንዲሁም የአይምሮው የጤንነት ሁኔታ ጤነኛ መሆን ይኖርበታል። ያለበለዚያ ግን ህጉ በሚያስቀምጠው ሥርዓት ወይም በወኪል በኩል ህጋዊ ግንኙነቶችን ለመፈፀም ይገደዳል። እንዲሁም በወንጀል ጉዳይ የወንጀል ህግን መሰረት በማድረግ ተጠያቂነትን ወይም ተከሳሽነትን ለመወሰን ወይም ሀላፊ እና ኢ-ሀላፊን ለመለየት የአንድ ሰው ችሎታ መኖር ወይም አለመኖር ማወቅ አስፈላጊ ነው።
ሰዎች ችሎታ የሚያጡበት ሁኔታ
በፍትሐብሄር ህግ ቁጥር 193 ስር እንደተደነገገው ጠቅላላ የችሎታ ማጣት ሁኔታ የሚያስከትሉ ምክንያቶች ዕድሜ ወይም የሰው አእምሮ ሁኔታ ወይም በተሰጠ የፍርድ ቅጣት ናቸው። በተጨማሪም የፍትሐብሔር ህጉ የተለየ የችሎታ ማጣት ሁኔታን የያዘ ሲሆን ይኸውም የተለየ ችሎታ ማጣትን ለመወሰን በግምት ውስጥ ለማስገባት የሚቻለው የሰውዬውን ዜግነት በመመልከት ወይም የሚያከናውነውን ሥራ መሰረት አድርጎ በመያዝ ነው። የችሎታ ማጣት አስረጂን በተመለከተ ሰው ሁሉ ችሎታ እንዳለው የሚገመት ሲሆን ይህ ሰው ችሎታ የሌለው ነው ብሎ ማስረዳት የሚገባው ሰውዬው ችሎታ የለውም ብሎ የሚከራከር ወገን ነው (የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 196)። ከተፈጥሮ ሰዎች በተጨማሪ የሰውነት መብት የተሰጣቸው ድርጅቶችና ለልዩ አገልግሎት የተመደቡ ንብረቶች ችሎታ ያላቸው መሆኑ የሚረጋገጠው እንደ አይነታቸው ለነዚሁ የሰውነት መብት በሚሰጧቸው ድንጋጌዎች መሰረት ነው። ችሎታ የሚያሳጡ ሁኔታዎችን እንደሚከተለው በዝርዝር እንመለከታለን።
በእድሜ ምክንያት ችሎታ ማጣት (Minors)
በእድሜያቸው ምክንያት ችሎታ የሌላቸው ሰዎች ወይም አካለመጠን ስላልደረሱ ሰዎች ሁኔታ በፍትሐብሔር ህጉ የተደነገጉት ድንጋጌዎች የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ ተፈፃሚ በሚሆንባቸው መስተዳድሮች ተፈፃሚ እንደማይሆን በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 319 ስር ተደንግጎ ይገኛል። በመሆኑም በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 215 ስር እንደተደነገገው በእድሜያቸው ምክንያት ችሎታ ያጡ ሰዎች ወይም አካለመጠን ያልደረሰ ሰውን በተመለከተ ትርጉም የሰጠ ሲሆን በትርጉሙ መሰረት አካለመጠን ያልደረሰ ሰው ማለት ፆታ ሳይለይ እድሜው አሥራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ልጅ ነው። በእድሜው ምክንያት ችሎታ ያጣ አካለመጠን ያልደረሰ ሰው ህጋዊ ግንኙነቶቸን በራሱ ማከናወን ህጉ ስለማይፈቅድለት ስለመልካም አስተዳደጉና ደህንነቱ ጉዳይ በአሳዳሪው የሚጠበቅ ሲሆን ንብረት ነክ ጥቅሞቹንና በአጠቃላይ የንብረቱን አስተዳደር በሚመለከት በሞግዚት ይወከላል (የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 216)። ስለአሳዳሪ እና ሞግዚት አስተዳደር በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ከአንቀፅ 215 እስከ 318 በዝርዝር ተደንግጎ ይገኛል።
በአእምሮ ሁኔታ ችሎታ ማጣት
አዕምሮዋቸው ስለ ጎደለ ሰዎች፡- የፍትሐብሔር ህጉ ትርጉም የሰጠ ሲሆን አዕምሮው ጎደሎ ነው የሚባለው በተፈጥሮ ዕውቀቱ ያልተስተካከለ በመሆኑ ወይም በአእምሮ መናወጥ ወይም በእርጅና ምክንያት የሚሰራውን ሥራ የሚያደረሰውን ለማወቅ የማይችል ነው። የአእይምሮ ደካሞች ሰካራም ወይም በመጠጥ አፍዛዥ በሆኑ ነገሮች ልማድ የተመረዙና ገንዘብ ያለ አግባብ የሚያባክኑ ሰዎች አእምሮዋቸው እንደጎደለ ሰዎች ይቆጠራሉ (የፍ/ሕ/ቁ. 339)።
በግልፅ ስለታወቀ የአእምሮ ጉድለት ያለበት ሰው፡- የአእምሮ ጉድለት ያለበት ዕብደቱ በግልፅ እንደ ታወቀ ሰው ሆኖ በህግ የሚቆጠረው ይህ የተባለው ሰው በሆስፒታል ውስጥ ወይም በአንድ የአእምሮ ጉድለት ያለባቸው ሰዎች መኖሪያ ቦታ ውስጥ በአእምሮው ሁኔታ ምክንያት በአንድ የጤና ጥበቃ ቤት ውስጥ ተዘግቶበት በዚህ በተዘጋበት ቦታ እስከሚቆይበት ጊዜ ነው (የፍ/ሕ/ቁ. 341)። በግልፅ የታወቀ እብድ የሚሰራቸውን ሥራዎች በተመለከት እብደቱ ግልፅ በሆነበት ጊዜና ቦታ ላይ የሠራቸውን ሥራዎች እርሱ ወይም ወኪሎቹ ወይም ወራሾቹ ሊቃወሟቸው ይችላሉ (የፍ/ሕ/ቁ. 343)። ተቃራኒ የሚሆን አስረጂ ከሌለ በቀር የነዚህ ሰዎች ሥራና ፈቃድ የውለታን ፈራሽነት የሚያስከትል ጉድለት ያለበት ነው ተብሎ ይገመታል። እንዲሁም በስህተት መገኘት ምክንያት የሥራዎችና የውሎች መፍረስ የሚመለከቱት የፍትሐብሔር ህግ ደንቦች በተመሳሳይ ተፈፃሚዎች ይሆናሉ (የፍ/ሕ/ቁ. 344)። ይሁንና የአእምሮ ጉድለት ያለበት ሰው ከእርሱ ጋር የተደረጉት ውሎች በመፍረሳቸው ምክንያት በቅን ልቡና በተዋዋዮች ሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ሀላፊ ይሆናሉ። በሌላ በኩል ከውል ውጪ ሀላፊነትን በተመለከተ ለጤናማ ሰው እንዳለው ሀላፊነት የሚኖርበት ከመሆኑ በተጨማሪ ይህ የአእምሮ ጉድለት ያለበት ያለ አግባብ ካገኘው ብልፅግና የተነሳ ላሉት ግዴታዎች ጤናማ ለሆነ ሰው ያሉበት ግዴታዎች ይኖሩበታል (የፍ/ሕ/ቁ. 350)።
የአእምሮ ጉድለት ያለበቱ በግልፅ ስላልታወቀ ሰው፡- የአእምሮ ጉድለቱ በግልፅ ያልታወቀ ሰው የፈፀማቸው የህግ ሥራዎች ውሎች በዚሁ ሰው የአእምሮ ጉድለት ምክንያት ሊሻሩ አይችሉም። ሆኖም የአእምሮ ጉድለት ያለበት ሰው እነዚህን ውሎች በፈፀመበት ጊዜ ጉድለት የሌለበት ፈቃድ ለመስጠት በማይችልበት ሁኔታ እንደ ነበረ ለማስረዳት ከቻለ ውሎቹን ለማፍረስ ይችላል (የፍ/ሕ/ቁ. 347)። የአእምሮ ጉድለቱ በግልፅ ያልታወቀ ሰው ወራሾች ወይም ባለገንዘቦች ይህ ሰው ለፈፀመው ውል ጉድለት የሌለበት ፈቃድ ቃል አልሰጠበትምና ውሉ ሊፈርስ ይገባዋል ሲሉ የአእምሮ ጉድለት ያለበቱን ምክንያት በማድረግ የውሉን መፍረስ ለመጠየቅ አይችሉም። ይሁንና የውል አድራጊው የአእምሮ ጉድለት ከተደረገው የውል ቃል የሚታወቅ እንደሆነ ይህ ደንብ ተፈፃሚ አይሆንም (የፍ/ሕ/ቁ. 348 እና 349)።
በፍርድ የሚደረግ ክልከላ (Judicial interdiction)
መከልከሉ ለጤናውና ለጥቅሙ የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝ አእይምሮው የታወከ ሰው/የፍትሐብሔር ህጉ እንደሚያስቀምጠው እብድ ሰው/ እንዲከለከል(እንዲጠበቅ) ዳኞች ፍርድ ለመስጠት ይችላሉ (የፍ/ሕ/ቁ.351)። እንዲሁም ስለ ዕብዱ ሰው ወራሾች ጥቅም ዳኞች የእብዱን መከልከል ሊፈርዱ ይችላሉ። በፍርድ ስለሚደረግ ክልከላ የክልከላ ውሳኔ እንዲሰጥ ዕብድ የሆነው ሰው ወይም ከባልና ሚስት አንዱ ወይም ከስጋ ወይም ከጋብቻ ዘመዶች አንዱ ወይም ዐቃቤ ህግ ሊጠይቅ ይችላል። ዳኞች የክልከላ ፍርድ ሲሰጡ በሚሰጠው ውሳኔ ውስጥ ጊዜውን በመወሰን የተባለው ሰው ዕብደት የጀመረው ከእንደዚህ ያለው ጊዜ ጀምሮ ነው ሲሉ ለማስታወቅ ይችላሉ። በተሰጠው ውሳኔ ውስጥ የተቆጠረው ቀን ስለ ክልከላው ከቀረበው ጥያቄ በፊት ከሁለት ዓመት የበለጠ ጊዜ ሊኖረው አይችልም (የፍ/ሕ/ቁ.352)።
በሌላ በኩል ዳኞች የክልከላ ፍርድ ሲሰጡ ወይም ውሳኔ ከሰጡ በኋላ የክልከላውን ውጤቶች ማጥበብ የሚችሉ ሲሆን ለተከለከለው ሰው እርሱ ራሱ እንዳንዶቹን ውሎች እንዲያደርግ ሊፈቅዱለት ይችላሉ። የተከለከለ ሰው የፈፀማቸውና ከስልጣኑ በላይ የሆኑት ሥራዎች መቃወም ይቻላል። እንዲሁም የተከለከለ ሰው ችሎታ የሌለው መሆኑን ከማያውቅ ቅን ልቦና ካለው ሰው ጋር ያደረገ እንደሆነ ውሉ በመፍረሱ ምክንያት በዚህ በቅን ልቡና በተዋዋለው ሰው ላይ ስለሚደርስ ጉዳት የተከለከለው ሰው አሳዳሪ በሀላፈነት ይጠየቃል (የፍ/ሕ/ቁ.374)።
በፍርድ የተከለከለ ሰው ጥበቃን በተመለከተ ለአካለመጠን ስላልደረሰ ሰው የሚደረግ ጥበቃ ማለትም በአሳዳሪና በሞግዚት የሚተዳደርበት ህግ ተፈፃሚ ይሆናል። በፍርድ ስለተከለከለ ሰው ክልከላ የማሳወቅ ግዴታ የአሳዳሪው ሲሆን ይህም የተከለከለው ሰው በሚኖርበት ቦታ ወይም ተቀማጭ ሆኖ እንዲኖር በተጠራበት ስፍራ ይሆናል። የተከለከለው ሰው አሳዳሪ ይህ የተከለከለ ሰው ችሎታ የሌለው ለመሆኑ በህግ መሰረት ማስታወቂያ በወጣበት ቦታ ተቀማጭ ሆኖ እንዲኖር መጠበቅ አለበት (የፍ/ሕ/ቁ.362)። የመኖሪያ ቦታውንም የለወጠ እንደሆን በአዲሱ መኖሪያ ማስታወቂያ እንዲወጣ ማድረግ አለበት። ይህን በፍርድ ከተከለከለ ሰው ጋር ህጋዊ ግንኙነት መፈፀም የሚፈልጉ ሰዎች ስለ ሁኔታው እውቀት እንዲኖራቸው እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።
በፍርድ የተከለከለ ሰው ህጋዊ ግንኙነቶች
ስጦታ፡-
የተከለከለ ሰው ሞግዚት በተከለከለ ሰው ስም ለተከለከለው ሰው ተወላጆች ልጆች ስጦታ ለማድረግ የሚችሉ ሲሆን እነዚህ ስጦታዎች በተከለከለው ሰው ቤተ ዘመድ ምክር ጉባኤ የተፈቀዱ ካልሆኑ በቀር ፈራሾች ናቸው (የፍ/ሕ/ቁ.367)።
ኑዛዜ፡-
የተከለከለ ሰው ክልከላው በፍርድ ከተነገረ በኋላ ኑዛዜ ለማደረግ የማይችል ሲሆን ከተከለከለበት ቀን በፊት የተናዘዘው ኑዛዜ ይፀናል። ነገር ግን የኑዛዜው ቃላት ለርትዕ ተቃራኒ መስለው ለዳኞች የታዩ እንደሆነና የተናዘዘውም የጤናው ሁኔታ ያስደረገው መስሎ የታያቸው እንደሆነ ዳኞቹ ኑዛዜውን በሙሉ ወይም በከፊል ፈራሽ ሊያደርጉት ይችላሉ(የፍ/ሕ/ቁ.368)።
ጋብቻ፡-
በፍርድ የተከለከሉ ሰዎች ፍርድ ቤት ካልፈቀደ በቀር የጋብቻ ውል መዋዋል አይችሉም። ከፍርድ ቤት ፍቃድ ውጪ የተደረገ የጋብቻ ውል በማንኛውም ጥቅሜ ይነካል በሚል ወገን ተቃውሞ ሊቀርብበት ይችላል (የፍ/ሕ/ቁ.369)። ፍቺና ልጅ መካድን በተመለከተ ያሳዳሪው ፍቃድ አስፈላጊ እንደሆነ የፍትሐብሔር ህጉ ይደነግጋል።
የክልከላ መቅረት
ስለክልከላ የተሰጠው ፍርድ ሲሻር የችሎታ ማጣት ፍፃሜ ሲሆን የክልከላው ውሳኔ መቅረት አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ከሞግዚት አስተዳደር መውጣት ያለው ውጤት ይኖረዋል። ይህም የሚሆነው ክልከላው እንዲወሰን ያደረጉት ምክንያቶች በቀሩ እና የተከለከለው ሰው ንብረቱን ለመምራት እና ለማስተዳደር ሲችል ነው። አእምሮው ከጎደለው ሰው በቀር ስለ ክልከላው ፍርድ እንዲሰጥ ለመጠየቅ የሚችሉ ሰዎች በማናቸውም ጊዜ የክልከላው ውሳኔ እንዲቀር ጥያቄ ለማቅረብ የሚችሉ ሲሆን አሳዳሪው ወይም ሞግዚቱም የክልከላው ውሳኔ እንዲቀር ለመጠየቅ ይችላሉ (የፍ/ሕ/ቁ.377)።
በህግ የተከለከሉ ሰዎች
በህግ የተከለከለ ሰው ማለት አንድ በወንጀል የተቀጣ ሰው በመቀጣቱ ምክንያት ንብረቶቹን እንዳያስተዳድር ህግ የከለከለው ሰው እንደሆነ የፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 380 የሚደነግግ ሲሆን አንድ ሰው በህግ እንደ ተከለከለ ሆኖ የሚቆጠርባቸው ሁኔታዎች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ተወስነዋል።
በህግ የተከለከለ ሰው አሳዳሪ የማይኖረው ሲሆን የንብረቶቹ አስተዳደር ዳኞች ለመረጡት ሞግዚት ይሰጣል(የፍ/ሕ/ቁ.382 እና 383)፡፡ በህግ የተከለከለ ሰው በፍርድ ከተከለከለ ሰው በተቃራኒ ጋብቻን ማድረግ፣ ፍቺ መጠየቅ፣ ልጅነት መቀበልና መካድ የሚችል ሲሆን ሞግዚቱ በህግ በተከለከለው ሰው ስም እነዚህን ሥራዎች መፈፀም አይችልም(የፍ/ሕ/ቁ.386)። በህግ የተከለከለው ሰው ያደረጋቸው ሥራዎች ወይም ውሎች ከስልጣኑ በላይ የሆኑ እንደሆነ ፈረሽ ናቸው። በህግ የተከለከለ ሰው ችሎታ ማጣትን ያስከተለው ቅጣት በተፈፀመ ጊዜ በህግ የተወሰነበት ክልከላ ቀሪ ይሆናል(የፍ/ሕ/ቁ.388)።
በአጠቃላይ ችሎታ ህጋዊ ግንኙነትን ለማከናወን መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን ማንኛውም ሰው ህጋዊ ግንኙነቶችን ከሰዎች ጋር ከመፈፀሙ በፊት የሚዋዋለው ሰው ችሎታ ያለው መሆኑን ማረጋገጥ በኃላ ላይ ሊከሰቱ ከሚችሉ እንደ ውል መፍረስ ካሉ ችግሮች የሚታደገው ስለሆነም ተገቢው ጥንቃቄ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።
የቴሌግራም ቻናል ቤተሠቦቻችን ቁጥር1K ደርሷል!! እርስዎም ይቀላቀሉና ወዳጅነታችንን በማጠናከር አዲስና አሥተማሪ መረጃዎችን ያግኙ!!
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ! https://t.me/jlrtinet
ሙሉ መረጃ ለማዉረድ ከህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ነው!

የስራ አስፈጻሚ ክፍሎች

አጫጭር መጣጥፎች

የስራ አስፈጻሚ ክፍሎች